በቤኒሻንጉል ክልል በሕዝብ ማመላላሻ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች ተገደሉ

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ

በምዕራብ ኢትዮጵያ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታጣቂዎች በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት ፈጽመው ቢያንስ 20 ሰዎች መግደላቸውን አንድ የክልሉ ኃላፊ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጥቃቱ ስለመፈጸሙ የሚያውቁና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ እኚህ የቤኒሻንጉል ክልል ከፍተኛ ኃላፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከመተከል ወደ ጉባ በመጓዝ ላይ በነበረ አውቶብስ ላይ ረቡዕ የካቲት 23/2014 ዓ.ም. ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጠዋል።

አፍሪካ እርሻ ልማት በሚባለው አካባቢ ላይ ያደፈጡ ታጣቂዎች በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ለጊዜው ትክክለኛው ቁጥር ባይታወቅም ከ20 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል።

ቢቢሲ ከክልሉ የፀጥታ አካላት ስለጥቃቱ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ያደረገ ቢሆንም ለጊዜው ምላሽ አላገኘም።

ኃላፊው እንዳሉት ጥቃቱ የተፈጸመው ከሱዳን በኩል ሰርገው በሚገቡ 'ፀረ ሰላም ኃይሎች' መሆኑን አመልክተው፣ ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ጥቃቶችን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ይፈጽሙ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከጥቂት ወራት ወዲህ ክልሉ ከፌደራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት በወሰደው መረጋጋት የማስፍን እርምጃ በአካባቢው በታጣቂዎች ሲፈጸም የቆየውን ጥቃት መቆጣጠር ተችሎ የነበረ መሆኑንም ኃላፊው ጠቅሰው የአሁኑ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የመጀመሪያው ነው ብለዋል።

በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን በሚመለከትም ከመተከል ወደ ጉባ የሚሄዱ የተለያዩ የኅበረተሰብ ክፍል አባላት መሆናቸውን እንጂ ስለማንነታቸው እስካሁን በዝርዝር የታወቀ ነገር የለም።

ጥቃቱን ተከትሎም የክልሉ ፀጥታ ኃይል ፈጻሚዎቹን ለመቆጣጠር እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ኃለፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የሚወሳን ሲሆን፣ በቅርቡ የኤልክትሪክ ኃይል ማመንጨት የጀመረው ግዙፉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ይገኝበታል።

ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃትን በመፈጸም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደሉ ሲሆን በርካታ ሺዎች ደግሞ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆነዋል።

ታጣቂዎች በሚፈጽሙት አሰቃቂ ጥቃቶች የተነሳ ከሁለት ዓመት ወዲህ አብዛኛው የክልሉ ክፍል በቤኒሻንጉል ክልል እና በፌደራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሚመራ የዕዝ ማዕከል [ኮማንድ ፖስት] ስር ሆነው ቆይተዋል።

የቤንሻንጉል ክልሉ ካማሺ፣ መተከል እና አሶሳ በሚሰኙ ሶስት ዞኖች የተዋቀረ ነው።

በቆዳ ስፋቱ ሰፊውን ክፍል የያዘው የመተከል ዞን የሕዳሴ ግድቡ መገኛ የሆነውን ጉባ ወረዳን ጨምሮ በውስጡ ሰባት ወረዳዎችን ይይዛል።

ከአማራ ክልል እና ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰነው ይህ ዞን በተደጋጋሚ ጥቃቶች የሚፈጸምባቸውን ቡለን፣ ድባጤ፣ ወንበራ፣ ፓዌ፣ ዳንጉር እና ማንዱራ ወረዳዎችን አቅፏል።

ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚዋሰነው ካማሺ ዞንም ከመተከል ሻል ያለ ሰላም ቢኖረውም በርካታ ሲቪሎች በተለያዩ ጥቃቶች ሲሸበሩ የቆዩበት ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታትም በርካታ ንፁኀን በታጣቂዎች መገደላቸው ከቀያቸው መፈናቀላቸው ተሰምቷል።